ዩቶፒያ
በ 2019 ዓ ም በ 21 ኛው አለም አቀፍ የአሻንጉሊቶች ቲያትር ፌስቲቫል ላይ ያለን ተሳትፎ
ዩቶፒያ! ይባላል የምንሳተፍበት መድረክ
ሁላችንም የወደፊት እጣ ፈንታችን ላይ ያተኮርን ያሳለፍናቸውን ተመክሮዎች ለወደፊቶቹ ተግባሮቻችን ግብአት ለማድረግ የምንጥር ፍጡሮች ነን። ይህ ትኩረቱን ሁሉ ነገ ላይ ያደረግ እሳቤ የሚገለፅባቸው የትየለሌ መንገዶች ሲኖሩ በተለይ ዛሬ ደግሞ ዲጂታል ዓለም እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትልቅ ቦታ እየያዙ ይገኛሉ። ሮቦቶችን በፊት የሰዎች በነበሩ የሥራ ቦታዎች ላይ መጠቀም፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በናኖ ቴክኖሎጂ አማካኝነት እስክ እያንዳንዱ ሕዋስ ጥግ ዘልቆ መግባት፣ እና ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎችን የማስተላለፍን ለሰው ልጆች በተለይ የተጠበቀ የአስፈፃሚነት ስልጣን ራሳቸውን ችለው ለሚሠሩና ሲብስም ለሰው ልጆች የመጨረሻው አደጋ ሊሆን በሚችል መልኩ ራሳቸውን ሊያባዙ ለሚችሉ ሮቦቶች አሳለፎ መስጠትን የመሳስሉ ልበ ወለድ ትርክቶችና የሳይንስ ፋንታሲዎች ስል ወደፊታችን ያለን እይታና ሥዕል ላይ ተፅእኖ ያደርጋሉ፣ የፈጠራ ፋንታሲዎች ቢሆኑም ተመሳሳይ ሕልሞች እንድናይ ምክንያት ይሆናሉ። ስለ ነገአችን በምንሰማቸው እነዚህ ትርክቶች ለይ ያሉን አግራሞቶች ተስፋንና ሃሴትን ብቻ ሳይሆን ፍርሃትንና ጥርጣሬዎችንም ያካትታሉ። እዚህ ላይ ከራሳችን አእምሮ የሚመነጩና በፈጠርናቸው ቴክኒካል ሜዲያዎች አማካኝነት ምሥልና ትርክት የሚያገኙ ፈጠራዎች ተመልሰው አስተሳሰባችን ላይ ተፅእኖ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ህዋን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋልና ማርስ ላይ የመኖር እድል ለሳይንስ ልቦለድ ቅርብ ቢሆኑም ምድራችን ላይ ሊኖረን የሚገባውን አትኩሮት በመቀነስ የዛሬና አሁን ተጨባጭ ህይወታችን መዋቅር ውስጥ ይገባሉ። የእድገትና ስልጣኔ ጣራና ውጤት አለማችንን ለቆ ወድ ህዋ መሰደድ ከሆነና በዚህም የሰው ልጆች ፍላጎቶች ከተፈጥሮና ላመጣጣቸን ካለን የእስካሁን ግንዛቤ ጋር ያላቸው ቁርኝት ከተካደ ምድራችንን ወሳኝ አደርጎ የማየት እሳቤ እየተሸረሸረ ይሄዳል። በሳይንስና ጥበብ አማካኝነት በአእምሮአችን የተወለደው ምናባዊ ዓለም ከምድራችንና ከሷ ጋር የሚያያዙ ችግሮች ጋር የምናደርገውን ግብግብ አላስፈላጊ በማስመሰል የስሜቶች ውጣ ውረድ የሌለበት፣ አልጋ ባልጋ የሆነና በሂሳብ ስሌት ተቀምሮ የሚቀመጥ የመኖር ትርጉም ቃል ለመግባት ይዳዳዋል።
የዚህ አይነቱ ስለ ሰው ልጆች የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀርብ ትንቢት ሃይሉ በዋናነት የሚመነጨው ልክ እንደ ካፒታሊዝም በተለያዩ ተፅእኖ ፈጣሪ ሃይሎች አማካኝነት የሰው ልጆች የእድገት ጉዞ አማራጭ የለሽ መዳረሻ እየተደረገ መቅረቡ ነው። ግን ይህ የነገአችን ትንቢት ምክንያቱ የተለመደውና የሰው ልጆች ተፈጥሮ የሆነው ለራስ ተግባር ሃላፊነት ያለመውሰድ ዝንባሌ ይሆን? ችግሮችን እየፈጠረ ያለውን በግለሰብ፣ ማህበረሰብና ቴክኖሎጂ መካከል ያለ የሃይል አሰላለፍ ላለመፈተሽ በዚህም ለተወሳሰቡ ና ብዙ አትኩሮታችንን ለሚሹ ተግዳሮቶች የማይጨበጡ የፋንታሲ መልሶች በመቸር የራሳችንን እድል በራሳችን የመወሰን ማህበረሰባዊና ዲሞክራሲያዊ ሃላፊነቶችን መሸሽ ይሆን?
ገና ስላልተገኘ የልበ ወለድ ዓለም እየተጠበብን በርግጠኝነት ያለችንንና ብቸኛዋን የመኖሪያ ምድራችንን መበደል ትልቅ ጥፋት አይደለምን? ፕላን ቢ ን ፈልገን ሳናገኝ ፕላን ኤ ን መጣል ሞኝነት አይደለምን? እያንዳንዳችን በመኖራችን ብቻና ከዚያ ደግሞ በአኗኗር ዘይቤአችን ለምድራችን መበላሸት እንደምናዋጣ ማወቅ ይገባናል። ስለሆነም የኢኮሎጂን ጥበቃ ከዋነኞቹ የሞራል ግዴታዎቻችን አንዱ ማድረግ ወሳኝ ነገር ነው። ነገሩ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነው። የእንስሳትና እፅዋትን፣ የተራሮችና ወንዞችን፣ የባህሮችና ጫካዎችን መብቶች ደንግጎ በውዴታ መጠበቅ ከተፈጥሮ ጋር ያስታርቀናል። የሰው ልጆች ሁሉ ተባብረን ከሃላፊነቶች ሁሉ ትልቁ የሆነውን ተፈጥሮን የመንከባከብና የመጠበቅ ሥራ መተግበር ግድ ይለናል።
እያንዳንዱ የሰው ፍጡር ተፈጥሮ የቸርችው ትልቅ የታመቀ አዎንታዊ ሃይል አለው። ይህንን እምቅ ሃይል በእውቀት፣ በተሞክሮና በጥበብ እያገዙ ምቹ የሆነ የመኖሪያ ከባቢን ለመፍጠር ምድራችን የገጠሟትን ችግሮች በጥልቅ መረዳትና እነዚህንም ችግሮች ለመቅረፍ ቁርጠኝነትና ቀጣይነት ያለው እንቅስቃሴ ያስፈልጋል። የፕሮጀክት ዩቶፒያም ተልዕኮ ከዚህ ጋር በተያያዘ ለአዲስ የሰዎች ሉዓላዊነት መፈጠር የሚበጁ መንገዶችና ዘዴዎችን በመጠቆም የዘመኑ ግኝቶች የሆኑትን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በዋናነት ተፈጥሮን ማገዣና መንከባከቢያ የሚሆኑበትን ስነ ልቦናዊ ድባብ ማመቻቸት ነው። የወደፊቷን ለሁላችንም ቦታ የምትሰጥ ብሩህ ዓለም ለማምጣት ጅምሮች፣ ስትራቴጂዎችና ጥረቶች ዛሬውኑና በያለንበት በግልፅ መታየት አለባቸው። አንተም፣ አንቺም፣ እኔም ዲሞክራሲን እየተገበርን ወደፊት እንዴት አብረን መኖር እንደምንፈልግ የምናሳይበት መድረክ ነው። በፕሮጀክት ዩቶፒያ መልስ የምንሰጠው ወደፊታችን ምን መምሰል አለበት ለሚለው ቁልፍ ጥያቄ ነው!
ረቡዕ ሜይ 29 ቀን 15 ሠዓት ኑረንበርግ ሎረንዘር ፕላትስ አርብ ሜይ 31 ቀን 15 ሠዓት ፉርት ሱድ ስታድት ፓርክ ቅዳሜ ጁን 1 ቀን 15 ሠዓት ኤርላንገን ሽሎስፕላትስ
Mit., Den 29.05 15 Uhr Nürnberg Lorenzer platz Fr. 31.05 15 Uhr Fürth Südstadtpark Sam. 01.06 15 Uhr Erlangen Schlossplatz
ግርዶሽ የተሰኘውን ድንቅ የመድረክ ቲያትር በ አድዋ ድል ፻፳፫ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ
Ein Stück über die Schattenseiten der neuen Freiheit in den sozialen Medien
አድዋ! የጥቁር ህዝቦች ድል
የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡ የመላው ዓለም ተፈጥሮአዊ ግብር እና ሰብአዊ ክብር የታደሠው፤ በእውነትና በፍትህ ህልውናና ምልዓት ላይ የተሰካ ትልቅ ጥርስ የተነቀለው … በአድዋ የታላቅ ህዝቦች ታላቅ ድል ነው፡፡
ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮጳ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጧል ይለናል የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ የአድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ በተሰኘና ዳኘው ኃይለሥላሴ ወደ አማርኛ በተረጐሙት መጽሐፉ ላይ፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ፈረሱ ላይ ሆኖ የጋሻውን እምብርት መሬት ላይ እያጠቀሰ ጐራዴውን አየር ውስጥ እየቀዘፈ ባበደ መንፈስ (በተቆጣና በቆረጠ መንፈሥ) በጀግንነት ተዋግቷል፡፡
ጦርነቱ በተጀመረ ከአምስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሃምሣ ስድስቱም የኢጣሊያ መድፎች ሙሉ ለሙሉ ተማርከዋል፤ የቅኝ ገዢውን ወራሪ ሠራዊት ከመሩት ጀኔራሎች ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከጥቂት አጃቢዎቹና በሽንፈት ከተበታተኑ የኢጣሊያ ወታደሮች ጋር ሸሽቷል፡፡
በማግስቱ የካቲት 24 ቀን 1888 ዓ.ም ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ የኢጣሊያ ምርኮኞች በምኒሊክ ድንኳን ፊት ሲያልፉ የኢትዮጵያ ጀግና የገበሬ ሠራዊት እየፎከረ እየሸለለ አሳልፉዋቸዋል፡፡ ጄኔራል አልቤርቶኒ በምርኮኛነት ኢትዮጵያ ውስጥ ቆይቶ አገሩ ከተመለሰ በኋላ በፃፈው መጽሐፍ ላይ ከሚፎክሩት ጥቁር የነፃነት ተዋጊዎች መሃከል አንዱ እንደ እኛው ነጭ አውሮጳዊ ነው ብሎአል፡፡ ይህ ሰው ከፈረንሣይ አገር ወደ ኢትዮጵያ ለጦር መሣሪያ ጥገና የመጣ ካፒቴን ኦርዲናንስ ሲሆን፤ አሁን ጊዜው የጦርነት ስለሆነ ወደ አገርህ ተመለስ ቢባል ቢሠራ አሻፈረኝ ብሎ ከእኛ ጋር አድዋ ድረስ የዘመተ ነው፡፡
ታላቅ በሰላምና በፍቅር የመደመር ቀን ለኑረንበርግና አካባቢው ነዋሪ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በሙሉ!
የተከበራችሁ እንግዶች *ክብራትና ክብራን*
የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ለረጅም ጊዜ በጋራ የኖሩ የጋራ ትስስር ያላቸው ህዝቦች ናቸው። ይህም ትስስር በሁለቱ ህዝቦች መሃከል ወንድማማችነትን፣ የጋራ የሆነ ባህልን፣ ኤኮኖሚንና ሌሎችን ህሴቶችን ፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል። ተፈጥሮ የነበረው ወንድማማችነት፣ ትስስርና መቀራረብ በተፈጠረው ችግር ላለፈው 20 ዓመት ተቋርጦ ቆይቷል።
ያለፈው 20 ዓመት በሁለቱም ሃገሮች ላይ በቀላሉ ሊገመት የማይቻል አሰቃቂ የሆነ የሰውም ሆነ የኤኮኖሚ እልቂትና ውድመት ፈጥሯል። በሁለቱ ህዝቦች ላይ ደግሞ ከባድ የሆነ ችግርና ተፅእኖ ፈጥሯል እንዲሁም ሊፈጠር የነበረ እድገትና ብልጽግና እንዳይቀጥል ሆኗል።
የተከበራችሁ እህትና ወንድሞች
ያለፈው 20 ዓመት ያስተማረን ትምህርት ቢኖር በአገሮች መካከል ሰላም ከሌለ በህዝቦች መካከል መጠራጠርን፣ አለመተማመንንና ተረጋግቶ አለመኖርን እንደሚፈጥር ያሳየናል። ይህም መጠራጠር፣ አለመተማመንና ተረጋግቶ አለመኖር መኖሩ ደግሞ የሁለቱ ሃገሮች ህዝቦች እድገት፣ ብልጽግናና አብሮ መስራት ሊኖሩ አይችሉም።
ይህንንም በመረዳት በሁለቱ አገሮች መንግስታት በተደረገው የሰላም ጥሪ የሁለቱ ሃገሮች ህዝቦች በሰላሙ ጥሪ መሰረት እንዲገናኙና እንዲወያዩ ወደፊት አብረው እንዲሰሩ ደረጃ በደረጃ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው።
እኛም በኑርንበርግና አካባቢው የምንገኝ የኢትዮጵያና የኤርትራ ኮሚኒቲ የዚህ የሰላም ጥሪ አካል በመሆን ይህን የተገኘውን ሰላም ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ የመጀመሪያውን ግንኙነት ሲያረግ ቆይቷል። ይህ ጅማሮ አዎንታዊ መልስ እንዲኖረው በማለት ይህን ዛሬ የምናከብረው በዓል በጋራ ለማዘጋጀት በቅተናል።
በሁለቱ ሃገሮች ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ሰላም እንዲቀጥልና ዘላቂነት እንዲኖረው እንዲሁም ለቀጣዩም ትውልድ እንዲተላለፍ ትልቅ ስራና ትግል ስለሚጠይቅ በኑርንበርግና አካባቢው የምንገኝ የሁለቱ ሃገር ዜጎች የሰላሙ አካል እንደመሆናችን መጠን ይህን የተጀመረውን ግንኙነት ዘለቄታ እንዲኖረው የሁላችን ተሳትፎ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለማስታወስ እወዳለሁ።
የተከበራችሁ እንግዶች
በሁለቱ ሃገሮች ህዝቦች ሰላም መስፈን እዚህ ኑርንበርግ ከተማ ለሚኖሩት የሁለቱ ሃገር ህዝቦች አብሮ ለመስራት የሚያደርገው አስተዋጾ ከፍተኛ ነው። በከተማችን የሁለቱ ሃገር ህዝቦች ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ቁጥር ከፍተኛውን ቦት ይይዛል። እዚህ ከተማ እንደመኖራቸው መጠን ለህብረሰባችን የሚያስፈልጋቸውን ትብብር የሚያስፈልጋቸውን ስራዎች አብረው ቢሰሩ የበለጠ የተሳካ ይሆናል።
ለምሳሌ በከተማው አስተዳደር የተጀመረው የአፍሪካን ማህበሮች በአንድ ጥላ ስር ለማደራጀት ጥሪ ላይ የሁለቱ አገሮች በጋራ ሲሰሩ ተሰሚነታቸው የላቀ ይሆናል።
በሁለቱ ሃገር መንግስታት የተጀመረው የሰላም ጥሪና አብሮ ለመስራት ፍላጎት በመከተል እዚህ ያለነው ሁለቱ ማህበራት ደግሞ የጀመርነውን አብሮ መስራት ቀጣይነት እንዲኖረው በኑርንበርግና አካባቢው የምንኖር የሁለቱ አገሮች ህዝቦች ተሳትፎ እንዳይለየን በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ሁለቱ ማህበራት ወደፊት አብረው ለሚያደርጓቸው ስራዎች የሁለቱ አገር ኤምባሲዎች ድጋፍና ትብብር በሚያስፈልግበት ጊዜ ትብብራቸው እንዳይለየን ስንል ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ለተባበሩን እህቶችና ወንድሞች በሁለቱ ማህበራት ስም ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ።
በመጨረሻ ሁለቱ ማህበራት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦች ሰላምን ፍቅርን አብሮነትን እንዲሁም ለሁለቱ አገሮች እድገትንና ብልጽግናን እንመኛለን።
የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦችን እግዚአብሄር ይባርክ!
አመሰግናለሁ!