በርጩማ ሆከርሌ

ስለ ኢትዮጵያ  ባህል ልምድና የአኗኗር ዘይቤ ስናስብ ቡናንና የቡና አቀራረብ በማህረሰባችን ውስጥ ያለውን ቦታ ማስታወስ የግድ ይለናል። የቡና ሴሬሞኒ በሀገራችን ተጐራባች ቤተሰቦችና የመንደሩ ሰዎች ዕርስ በርስ ጊዜ የሚሰጣጡበት፣ስለችግሮቻቸውም ሆነ በማህበረሰቡ ዘንድ አነጋጋሪ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ የሚለዋወጡበት፣በተወሰነ ደረጃም የጋራ ግንዛቤ የሚያዝበት መድረክ ነው።በዚህ በምንኖርበት የዓለም ክፍል ደግሞ ስልጣኔ የሚያስከፍለው ትልቍ ዋጋ ሰዎች ለሌች ቀርቶ ለራሳቸውም የሚሆን ጊዜ ማጣት እንደመሆኑ ቡናም እኛ ጋር የነበረው ክብር ተገፎ በወረቀት ብርጭቆ መንገድ ለመንገድ ሁሉ ሲጠጣ ታዝበንና ለራሳችን ባህላዊ የቡና አቀራረብ ያለን አክብሮት ከፍ ብሎ ይህን ልምድ ለማስተዋወቅና ከፍ ከፍ ለማድረግ መስራት ጀመርን።

 

የመጀመሪያ ስራ  የኛን አገር የቡና አቀራረብ ከሚያሳምሩ ነገሮች ዋና ዋናዎቹን ብዙ ወጪ በማይጠይቅ፣ክብደትና የቦታ ስፋት የሌለውና በትራንስፖርት ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የማያስቸግር  አድርጎ መስራት የመጀመሪያ ስራችን ነበር። በዚህ መስፍርት  ቢቢሲዖ የሜሴ ዲሳይን ቢሮና (bbco messe design)  ሬሃኡ (Firma REHAU) የሚባሉ መስሪያ ቤቶች በነጻ በለገሱን የፕላስቲክ ማቴሪያሎች አንድ መቶ በርጩማዎችና ሁለት ዲያሜትራቸው 3 ሜትር የሆነ ክብ የለምለም ሳር ምንጣፎች ፉርት በሚገኘውና ነጻ ትብብሩን በፈቀደልን የላይፍ ሾለር ሞዴል ስራ ስቱዲዮ ሰራን። በነዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በአዳራሽ ውስጥና  የውጭ የድንኳን ውስጥ ዝግጅቶች የሀገራችንን የቡና አጠጣጥ ባህል አሳየን፣ ከፍተኛ ተወዳጅነትም አተረፈ።

 

 

መላመድ

ሁለተኛ ስራ  የመላመድ  ጎጆ  “ዓለም ”  በአፍሪካ ፌስቲቫል 2014 እና 2015 በድንኳናችን ውስጥ ያየነው የህዝብ ትርምስ ይህ ጎጆ የበለጠ ዓምሮና አድጎ ሁነኛ የሰዎች መቀራረቢያ ና መለማመጃ መድረክ መሆን እንደሚችል አሳየን።  የምድርን(ግሎቡስ)ቅርጽ የያዘ ልዩ ኩፖል ወይንም ዶም የመስራት ሀሳብም መጣልን።  እንዳጋጣሚ ሆኖ የጀርመን ፌደራል መንግስት የቤተሰብ ሚኒስቴር 2015 ላይ “ዲሞክራሲን መኖር” በሚል ርእስ የተለያዩ ማህበራት የፈጠራ ስራ ውድድር አውጥቶ ነበርና እኛም ሀሳባችንን በፕሮጀክት መልክ አቅርበን ከ25 ተወዳዳሪ ማህበራት የመጀመሪያውን ቦታ ለመያዝ ቻልን። ባገኘነው የፋይናንስ ድጎማና በድጋሚ የፊርማ ሬሀኡ ባደረገልን በርካታ የፕላስቲክ ቱቦዎች ልገሳ በመታገዝ ሶስት ወር ከቆየ የፈጠራና የኮንስትራክሽን ዎርክ ሾፕ በኋላ በ19.09.2015 የመላመድን ዶም/ኩፖል ለማስመረቅ በቃን።

 

 

የተስፋ ችግኞች ፕሮጀክት
Schulnachhilfe für bedürftige Kinder & Jugendliche

አጭር የፕሮጀክቱ ገለፃ

በስደት ኑሮ በሚመሠረቱ ቤተስቦች ውስጥ የሚወለዱ ህፃናት እድሜአቸው  ለትምህርት ቤት ሲደርስ ከባለ ሀገሮቹ ህፃናት የበለጠ ጫና ይፈጠርባቸዋል። ይህ የሚሆንበት ዋና ዋና ምክንያቶችም አንደኛ በቤት ውስጥ የሚነገረው ቋንቋ ከትምህርት ቤቱ ቋንቋ መለየትና ወላጆችም ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ልጆች ሊገጥማቸው የሚችሉ ተግዳሮቶች ላይ ራሳቸው በቂ ድጋፍ መስጠት ስላማይችሉ፣ ሁለተኛ ከፋይናንስ አቅም ውስንነት በተያያዘ ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ተጨማሪ የትምህርት ድጋፍ በተቀጣሪ አስተማሪ አማካኝነት ማቅረብ አለመቻል ናቸው።

ይህንን በኮሚኒቲአችን ውስጥም ትንሽ በማይባል መልኩ ያለን ችግር ለመቅረፍ ለተመሳሳይ ችግሮቻቸው ከኛ ቀድመው መልስ ማፈላለግ ከጀመሩ ማህበራት ልምድ ለመውሰድ የተስፋ ችግኞች  ፕሮጀክትን ቀረፅን። በኮሚኒቲአችን ውስጥ ቀደም ብለው ከመጡ ቤተስቦች የተውጣጡና በጥሩ ዉጤት የትምህርት ቤት ቆይታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ያሉ ወጣቶቻችንን በማነሳሳትና ግሎባል ኤልተርን ከሚባል በመስኩ የ አስር ዓመታት ልምድ ካካበተ ማህበር ጋር በመተባበር ከአንድኛ እስከ አራተኛ ክፍል ላሉ አዲስ ታዳጊ ህፃናት ዘውትር ቅዳሜ ከ 11 እስከ 14 ሠዓት የትምህርት ድጋፍ መስጠት ጀመርን። በዚህ ፕሮጀክት ህፃናት ድጋፍ ከማግኘታቸው በተጨማሪ ወጣቶቹም ወደፊት ራሳችንን ችለን ኮሚኒቲው በዚህ መስክ ያሉበትን ችግሮች ማሸነፍ የምንችልበትን ክህሎቶችና ባጠቃላይም ሀላፊነት ወስዶ ማህበረሰብን ማገልገልን እንዲለማመዱ፣ በተለያዩ ማህበራት መካከለም ለጋራ ዓላማ አብሮ መስራት፣ ልምዶችን መለዋወጥና አቅሞችን መደመር ምን እንደሚመስል በተግባር እንዲኖሩት አስችሏል።  

 

የፕሮግራሙ ስፋት ይዘትና ቀጠሮዎች:

ኮርሶቹ ለሦሥት ግሩፖች እያንዳንዳቸው ከአንድ አስተማሪና አንድ ታዳጊ ሜንተር ይኖራቸዋል.

በሳምንት 4 የትምህርት ሠዓታት ለእያንዳንዱ ግሩፕ ይሰጣል

ፕሮግራሙ ለ 13 ሳምንታት ይቀጥላል ( 28.04.2018 እስከ 21.07.2018)

የተስፋ ችግኞች ራስን መቻል

ለስድስት ወራት ያክል የዘለቀውን በኑረንበርግ የኢትዮጵያ ባህል ማህበርና ግሎባል ኤልተርን ማህበር ትብብር የተካሄደ የትምህርት እርዳታ ፕሮጀክት እንዳጠናቀቅን ከአንድ ወር እረፍት በሗላ ፕሮጀክቱን ራሳችንን ችለን ቀጥለናል። ፕሮጀክቱ በታዳጊዎቹም ሆነ በወላጆች ዘንድ ትልቅ ቦታ ስለተሰጠውና የተጠቃሚ ኢትዮጵያውያንን የብዛት መጠንና እንዲሁም ያሉንን ብዙ ሜንተሮች ፖተንሻል ከግምት በማስገባት የማንም ተቀጥላ ሳንሆን በራሳችን ፕላንና ሀሳብ ፕሮጀክቱን ማስኬድ እንደምንችል እናምናለን። ከትምህርታዊ ጥናት በተጨማሪም ታዳጊዎቹ በፈጠራ ስራዎች ላይ ይሳተፋሉ። ምስሉ ላይ የሚታየው ልጆቹ በ 13.10.2018 የመላመድን አዲስ ሽፋን ለማስዋብ በተዘጋጀ ዎርክ ሾፕ ላይ ከትምህርት ጥናት ጊዜ በሗላ የፈጠራ ችሎታቸውን ሲያሳዩ ነው። ለጊዜው በነፃ እንድንገለገልበት የተፈቀደልን ጋርተን ስትራሴ የሚገኘው የአቮ አዳራሽም ለትምህርት አሰጣጡ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ስላለው አቮን እናመሰግናለን።

 

 

የተቃርኖዎች ዓለም

ሰዎች ብዙ ስለ ተቃርኖዎች ያወራሉ …  አምላክ የፈጠረው ግን ብዝሃነትን ነው።. የኑረንበርግ ኢትዮጵያውያን ባህል ማህበርና የቱርክ ኩርዶች የወጣቶች ድምፅ ማህበር ቀለማትንና ጣእማትን እንደ ምሳሌ በመጠቅም ይህንን የተፈጥሮ እውነታ ያሳያሉ።  የተለያዩ ቀለማት፣ ጣእሞችና ሽታዎች ተደምረው የሚያፈዝ ውበት እንዲሁም  ነፍስን የሚያስደስት ሃርሞኒ ይፈጥራሉ!

በ 11082018 የኑረንበርግ ኢትዮጵያውያን ባህል ማህበር ከዋልያ ስፖርት ክለብ ተጫዋቾች ጋር በመሆን ባዘጋጀው ያንድ ቀን ዎርክ ሾፕ አዲሱ የመላመድ ድንክዋን ሽፋን ተጨማሪ ውበትና የመልእክት ማስቀመጫ ቦታ አገኘ። ልዚህም 105 ትሪአንግሎች መሃላችው ላይ ክብ ነጭ ሰርክሎች ተትተው እነዚህ ላይ ተሳታፊዎች ወይንም ታዳሚ እንግዶች አስፈላጊ ወይንም ጠቃሚ የሚሉትን መልእክት በማስተላለፍ በቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆኑ ይደረጋል።

ታዳጊ ህፃናቶቻችንም  በፈጠራ ስራዎች ላይ ይሳተፋሉ። ፎቶዎች ልጆቹ በ 13.10.2018 የመላመድን አዲስ ሽፋን ለማስዋብ በተዘጋጀ ዎርክ ሾፕ ላይ ከትምህርት ጥናት ጊዜ በሗላ የፈጠራ ችሎታቸውን ሲያሳዩ ያሳያሉ።